ጦርነት ይብቃን…!
ከሻዕቢያ ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መውጋት “ታሪካዊ ስህተት” እና ከፍተኛ “የሀገር ክህደት ወንጀል” ነው! ጦርነት ይብቃን…!
በጤና ችግርና ተመሳሳይ ነገር ደጋግሞ መናገርን በመሰልቸት ምክንያት ለአለፉት አምስት ወራት ገደማ ራሴን ከመገናኛ ብዙኃን አርቄ ነበር። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ከነበርኩበት በተሻለ የጤና ሁኔታ ላይ አይደለሁም። ሆኖም ሰላማዊ መፍትሄ ተነፍጎት ትውልድን እያስጨረሰ፣ ሀገርንና ሕዝብን እያደኸየ፣ አንድንነት እየበጣጠሰ ከሚገኘው ከወቅቱ የእርስ-በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ የሻዕቢያ ጦር በሙሉ ኃይሉ “ኢትዮጵያን” ዳግም መውረሩን በዜና ስሰማ ክስተቱን በዝምታ ማለፍ ተሳነኝና በጉዳዩ ዙሪያ ያለኝን የግል አመለካከትና አቋም በዚህች አጭር መጣጥፍ ለመግለፅ ፈለግሁ። ቀደም ሲል በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ወቅቱ ኢትዮጵያውያን ከአርቆ-አሳቢነት፣ ከሀገር ወዳድነት፣ ከሕዝብ አብሮነት፣ ከስብዕናም ሆነ ከሞራል አኳያ በዝቅጠት ደረጃ ላይ የምንገኝበት ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንድ ታሪካዊ ጠላት ከሆነው ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አብረን የራሳችን አካል የሆነውን የትግራይ ሕዝብን ለማጥቃት መሞከር እንኳንስ በተግባር ልንፈፅመው ቀርቶ በሃሳብ ደረጃ ሊነሳና ልንወያይበት የሚገባ ቁምነገር አልነበረም። በዚህ ዘመን ይህ መሆኑን ሳስብም በግሌ የወቅቱ የፖለቲካ ሂደት አካል በመሆኔ እጅግ ጥልቅ የሆነ ሀዘንና ከፍተኛ ቁጭት ይሰማኛል። ከሌሎችም ሆነ ከራሳችን ሀገር የፖለቲካ ታሪክ እንደምንገነዘበው በአንድ ሀገር ውስጥ የእርስበርስ ጦርነት ሲከሰት ተፋላሚ ወገኖች አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለማግኘት ሲሉ ከውጪ መንግሥታት የገንዘብ፣ የትጥቅ፣ የባለሙያ፣ የስልጠና ወይም የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማግኘት መሞከራቸው የተለመደና የሚጠበቅ ነው።
ነገር ግን በጠላትነቱ ከሚታወቅ አንድ የጎረቤት ሀገር መንግሥት ጋር በአንድ የጦርነት ግንባር ተሰልፎ የራስን ሀገርና ሕዝብ በግልጽ መውጋት ያልተለመደና የማይገባ ድርጊት ብቻ ሳይሆን እጅግ አሳፋሪ የሆነና የተሳሳተ አዲስ የታሪክ ክስተት ነው። ኢትዮጵያውያን በጎላ ሁኔታ የምንታወቅበት ታሪክ የውጪ ወራሪ ኃይል ሲመጣብን የውስጥ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተውና በአንድነት በመቆም ሀገርን ከጥቃት በመከላከል ነው፡፡ ከጠላት ጦር ጋር በአንድ ግንባር ተሰልፎ የራስን ግዛትና ሕዝብ መውረር የኛ መንግሥታት ታሪክ መገለጫ ሆኖ አያውቅም። ከጠላት ጋር ተሰልፈው ሀገርን የሚወጉ አንዳንድ አካባቢያዊ ኃይሎች ወይም ግለሰቦች በየዘመኑ ባይጠፉም በሥልጣን ላይ የሚገኝ የአንድ ሀገር መንግሥት ራሱ የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ጠላት የሆነ ሌላ የውጪ ኃይል ጋብዞ እና በራሱም ሆነ በጠላት ግዛት በኩል በአንድ ግንባር አብሮ ተሰልፎ ሲወጋ ማየት ግን በዶ/ር ዐቢይ ዘመን ብቻ ሲሆን የታየ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት የአሁኑንም ሆነ የመጪውን ትውልድ አንገት የሚያስደፋ እና አሳፋሪ የታሪክ ገፅታችን ሆኖ ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡ አንዳንድ በጭፍን የሕዝብ ጥላቻና በሥልጣን ጥም የታወሩ ግልብ የፖለቲካ ሰዎችና “ማህበራዊ አንቂዎች” ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል እንዳልሆኑ በመቁጠር የወቅቱን የሻዕቢያ ወረራ በትግራይ ወይም በሕወሓት ላይ ብቻ የተቃጣ እንደሆነ፣ ይህን የሻዕቢያ ጣልቃገብነትም ሀገርን የሚጠቅም ድርጊት እንደሆነ አድርገው እንደሚያዩት ግልፅ ነው። ሆኖም ከጊዜያዊ የጥላቻ ስሜት ርቆና የሀገርንና የሕዝብ ጥቅምን አስቀድሞ ሁኔታውን ለመገንዘብ ለሚፈልግ ለማንኛውም ቀና ዜጋ የወቅቱ የሻዕቢያ ወረራ በኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ጥቃት ጦርነት ይብቃን…! –
ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን እስከ-ወዲያኛው መዳን በማትችልበት መጠን የማፍረሱ ሴራ አካል መሆኑን መገንዘብ አይሳነውም። በግልፅ ሊናገሩት ባይደፍሩም ፕሬዚደንት ኢሳያስን የኢትዮጵያ ችግሮች የመፍትሄ አካል አድርገው ለማሳየት የሚሞክሩት ፖለቲከኞችም ይህንን እውነታ ይረዱታል። ሆኖም የእነዚህ ኃይሎች ፖለቲካ – ሲበዛ በትግራይ ሕዝብ፣ ሲያንስ ደግሞ በሕወሓት ላይ ባላቸው የጥላቻ አስተሳሰብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ ከምክንያታዊነት ጋር የተጣላ ነው፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ለጥላቻ ያላቸው ተገዢነት ለሀገሪቱና ለሕዝቡ አለን ከሚሉት ፍቅር የበለጠ በመሆኑ ምክንያት ገሃድ የሆነውን ሃቅ በጭፍን ሊክዱት መርጠዋል። በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት በእርግጥም ከኢትዮጵያ ህልውናና ደህንነት ጋር የተያያዘ ፍትሃዊ የሕዝብ ጦርነት ቢሆን ኖሮ በቀላሉና በአጭር ጊዜ በመንግሥት አሸናፊነት በተጠናቀቀ ነበር። የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት፣ የሕዝብ ብዛትም ሆነ የሃብት ልኬቱ ከ5% ያልበለጠ ድርሻ ያለውንና በራሱ ግዛት ስር የሚገኘውን የትግራይ ክልል በራሱ አቅም መቆጣጠር ተስኖት ያለምንም ሃፍረት ከሻዕቢያ ጨፍጫፊ ሰራዊት ጋር ተባብሮ የራሱን ሀገርና ሕዝብ ለመውረር የተገደደው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይህ የሆነው ጦርነቱ ከጭፍን ጥላቻና ከፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ባለፈ ምንም ዓይነት ሌላ አሳማኝ ሀገራዊ ምክንያት የሌለው ከንቱ ጦርነት በመሆኑ ነው።
ይህንን እውነታ በመረዳት ማንኛውም ለሀገሩ ህልውና፣ ለሕዝብ ደህንነትና ዘላቂ ሰላም ተቆርቋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የወቅቱን የሻዕቢያ ወረራ በግልፅና በድፍረት ማውገዝና፣ ከዚያም ባለፈ ወረራው በተግባር እንዲቀለበስ አቋም ይዞ ሊታገል ይገባል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በዋናነት ደግሞ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የቅርብ ጎረቤት፣ የባህልና የህልውና ተጋሪ የሆነው የአማራ ሕዝብ የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆኖ የሻዕቢያን ወረራ በመደገፍ የራሱንም ሆነ የሀገሪቱን የወደፊት ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ታሪካዊ ስህተት ከመስራት መታቀብ አለበት። እንዲህ ዓይነት ከራስም ሆነ ከሀገር ዘላቂ ጥቅም ጋር የሚቃረን ስህተት መስራት በገሀር ወዳድነቱና በፍትህ አዋቂነቱ ለሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ታሪክና ማንነት ፈፅሞ የማይመጥን ነው።
ሻዕቢያ ከአማራ ሕዝብ ጋር መቼም ቢሆን ከሕወሓትም ሆነ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከነበረው የበለጠና የቀረበ የወዳጅነት ታሪክ ኖሮት አያውቅም። እንዲያውም ሻዕቢያ በዋና ጠላትነት ፈርጆ በቋሚነት ሲታገል የኖረው የአማራን ሕዝብ ነው። ሻዕቢያ ዛሬ የትግራይ ሕዝብን የማንበርከክ ምኞቱ በለስ ቀንቶት ቢሳካለት ነገ ቀጣዩ የሻዕቢያ የጥቃት ዒላማና ተረኛ የአማራው ሕዝብ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የአማራንና የትግራይን ሕዝብ እርስ-በርስ በማዋጋትም ሆነ በየተራ እየወጉ ለማዳከም የሚደረገው ይህ ሙከራ በጊዜያዊ ሁኔታ ወይም በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን የሻዕቢያ የረዥም ዘመናት ኢትዮጵያን የማዳከም ፕሮጀክት አካል ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ እያወቅንም ይሁን ሳናውቅ የዚህ የጥፋት ፕሮጀክት ተባባሪ ሆኖ መገኘት ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው፡፡ በእኔ እምነት የትግራይ ሕዝብ ህልውና መቀጠል በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ የአማራ ሕዝብም ሆነ የአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊት ዋስትና ነው። የአማራ ሕዝብ ይህንን እውነታ በስክነት ተገንዝቦ ለራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና ህልውና ሲል የወቅቱን የሻዕቢያ ወረራ ከማንም በላይ መቃወምና ማክሸፍ አለበት። የሻዕቢያን ወረራ ደግፎ በመቆምና የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ተባባሪ በመሆን ይቅርና፣ በወቅቱ የእርስ-በርስ ጦርነት ተሳታፊ ሆኖ በመቀጠልም የአማራው ጦርነት ይብቃን…!
ሕዝብ የበለጠ ችግሩንና ተጠቂነቱን ያባብሰዋል እንጂ ጥቅሙንና ህልውናውን የማስጠበቅ ዕድል አይኖረውም። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በተግባር የታየውም ይኸው እውነታ ነው። በወቅቱ ፖለቲካም ሆነ በዚህ ጦርነት የአማራው ሕዝብ ለበለጠ መራቆት፣ መፈናቀልና እልቂት ከመዳረግ ባለፈ የትኛውም ዓይነት ችግሩ እንኳንስ ሲፈታ ሲቃለልም አልታየም። የአማራ ሕዝብ በዚህ ጦርነት መቀጠል ወደፊትም ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያገኝ አይችልም፡፡ የጦርነቱ ግብ ተደርገው እየተጠቀሱ ያሉት “ሕወሓትን ትጥቅ የማስፈታትም” ሆነ “ሕወሓትን ከምድረ-ገፅ የማጥፋት” ዓላማዎች ቢሳኩም ባይሳኩም የአማራን ሕዝብ መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት አያስችሉም፡፡ የአማራ ሕዝብ በፌደራል ደረጃ “በኦሕዴድ-ብልጽግና”፣ በክልል ደረጃ “በብአዴን-በልጽግና” በተመሳሳይ ሕግ እና ስርዓት እየተገዛ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት ያለውን ሕወሓትን በተለየ ሁኔታ ትጥቅ ለማስፈታትና ለማጥፋት መሞከርም የሚካሄደውን ጦርነት ፍትኃዊና ውጤታማ ሊያደርገው አይችልም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ አንድን አካል ብቻ ነጥሎ የማጥቃት ዓላማ ፍትኃዊ ካለመሆኑም በላይ አሁን ላይ በትግራይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የትግራይን ሕዝብ ሳያጠፉ ይህንን ዓላማ ፈፅሞ ማሳካት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የአማራው ሕዝብ ሲችል – ወንድሙ ከሆነው የትግራይ ሕዝብ ጋር በጋራ በመቆም ለዘላቂ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት መስራት፣ ለጊዜው ይህንን ማድረግ ከተሳነው ደግሞ – ቢያንስ የሌሎች ሴራና ደባ መጠቀሚያ ባለመሆን ለራሱና ለሀገሩ ዘላቂ ህልውና መጠበቅ የበኩሉን አዎንታዊ ድርሻ መወጣት ይኖርበታል።
የትግራይ ሕዝብም ዘላቂ ሰላም ሊያገኝና ህልውናው ሊጠበቅ የሚችለው ሁል ጊዜ ከዙሪያ ገባው ጋር እየተዋጋ በመኖር ሳይሆን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጎ ግንኙነትና አብሮነትን በመፍጠር መሆኑን በመገንዘብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላምና ለእርቅ ሂደት ልባዊ ተነሳሽነትና ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። የትግራይ የፖለቲካ ልኂቃን የአማራውን የፖለቲካ ማህበረሰብ በተመለከተ ሲያራምዱት የኖሩት አቋም ስህተት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ ይመስላል የአማራን ሕዝብ በተመለከተ በቅርቡ እያሳዩት ያለው የትርክት ለውጥ በአዎንታ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ሆኖም በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ መቃቃር በቀላሉ ሊሽር ስለማይችል ይህ የትርክት ለውጥ ከጦርነት ጊዜ ፕሮፖጋንዳና ታክቲክ ጋር የተያያዘ ጊዜያዊ የስልት ለውጥ ሳይሆን ልባዊና ዘላቂ ስትራቴጂካዊ የአቋም ለውጥ መሆኑን ሊያረጋግጥ በሚያስችል መጠን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የአማራው የፖለቲካ ማህበረሰብም ካለፈው ብሶቱ በላይ የአሁንና የወደፊት ጥቅሙን በማስቀደም የትግራይን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት በተመለከተ ተመሳሳይ ገንቢ አቋሞችን በመያዝና በማራመድ የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ወደ ጤናማ አቅጣጫ እንዲያመራ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት። በወቅቱ የእርስ-በርስ ጦርነት መቀጠል እንኳንስ የችግሩ ቀዳሚ ሰለባ የሆኑት የትግራይና የአማራ ሕዝቦች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይሆንም። ከዚህ ጦርነት አትራፊና ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት በትግራይ ሕዝብ ጥላቻ የሰከሩና ‘የጠላቴ ጠላት ወዳጄ’ በሚል ግልብ አስተሳሰብ የሚመሩ ጥቂት ፖለቲከኞችና “ማህበራዊ አንቂዎች”፣ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት የሥልጣን ዕድሜአቸውን ለማራዘም የሚጥሩ ጥቂት የመንግሥት ጦርነት ይብቃን…!
ባለሥልጣናትና ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ማዳከምና ማፍረስን የህይወት ዘመን ተልዕኳቸው ያደረጉ የሻዕቢያ መሪዎች ብቻ ናቸው። የወቅቱ የሻዕቢያ ወረራ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ ሕዝብም የሚጠቅም ፋይዳ የለውም። ሻዕቢያ በዚህ የወረራ ተግባሩ አሸናፊ የመሆን ዕድል ቢያገኝ የኤርትራ ሕዝብ ጭቆናና ሰቆቃ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመገንዘብ የኤርትራ ሕዝብም የዚህ ወረራ ተጋሪ ሳይሆን ተቃዋሚ ሊሆን ይገባዋል። የኤርትራ ሕዝብ በሻዕቢያ ቋሚ የጦርነት ፖሊሲ እየተመራ መቼም ቢሆን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ተቋዳሽ መሆን እንደማይችል በውል ሊገነዘብ ይገባል፡፡ እንዲያውም ጦርነቶች አንዳንድ ጊዜ ፈፅሞ ያልተጠበቀ ውጤት ፈጥረው የመጠናቀቅ ባህሪ ስላላቸው ይህንን ጦርነት የኤርትራ ሕዝብ እንዴት አድርጎ ለራሱ ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ አዲስ ዕድል ሊፈጥርበት እንደሚችል በአትኩሮት ሊያስብበትና ሊጠቀምበት ይገባዋል። በአጠቃላይ የወቅቱ የሻዕቢያ ወረራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የደፈረና ዓለም-አቀፍ ሕግን የሚፃረር ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው። ከዚህም በላይ፣ ይህ ወረራ በውጤቱ በትግራይ ሕዝብ ህልውናና በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ላይ ዘላቂ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ድርጊት ነው።
ስለሆነም ይህ ወረራ በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በኤርትራ ሕዝብና በዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ በግልፅ ሊወገዝና ሊቀለበስ ይገባል። በተለይም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሆኖ ይህንን የሻዕቢያ ወረራ በተግባር መተባበር ይቅርና በሃሳብ ለመደገፍም ቢሆን መሞከር ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሀገር ክህደት ወንጀል መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። በጦርነቱ መቀጠልና በሻዕቢያ ጣልቃ-ገብነት የትግራይና የአማራም ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ችግር የበለጠ የመባባስና የመወሳሰብ እንጂ የመለዘብም ሆነ የመፈታት ዕድል የለውም፡፡ እንዲያውም የወቅቱ ጦርነት አሁን በሚታየው ክብደት ለወራት ከቀጠለ ሀገር ተረካቢው ወጣት ትውልድ በታሪካችን አይተነው በማናውቀው መጠን ያልቃል፣ ሀገሪቱም ሆነች ሕዝቧ በድህነት አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃሉ፣ በሂደትም ሀገረ-መንግሥቱ በቀላሉ ተመልሶ መጠገን በማይችልበት መጠን ሊፈራርስ ይችላል፡፡ እንደ ሕዝብና ትውልድ ፍላጎታችንን እና ጥቅማችንን በአግባቡ ለማወቅ የሚያስችል የእውቀት እንጥፍጣፊ ቀርቶን ከሆነ ይህንን አውዳሚና ዓላማ-ቢስ ጦርነት በአስቸኳይ ማቆም አለብን፡፡ በእልህ፣ በጀብደኝነትና በጥላቻ ታውሮ በእንዲህ ዓይነቱ አውዳሚ የእርስ-በርስ ጦርነት ውስጥ መቀጠል የድንቁርና እና የኋላ-ቀርነት መገለጫ እንጂ የአዋቂነትም ሆነ የጀግንነት መለኪያ አይደለም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን የሁላችንም ችግር በሁለንተናዊ መልኩ እና በዘላቂነት መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው “ጦርነት ይብቃን!” በማለትና እጃችንን በሙሉ ልብ ለሰላም በመዘርጋት ብቻ መሆኑን ነው፡፡
ልደቱ አያሌው
መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም