የሞተው ፈረስ ፅንሰ-ሀሳብ: በጥበብ እውነታን መቀበል!!

የሞተው ፈረስ ፅንሰ-ሀሳብ: በጥበብ እውነታን መቀበል!!
ግልጽ የሆኑ ችግሮችን እንደማይፈቱ ረቂቅ ምስጢሮች የመመልከትን የተሳሳተ አዝማሚያ የሚጋያልጥ ምፀታዊ ዘይቤ “የሞተው ፈረስ ፅንሰ-ሀሳብ” ይባላል፤ ወይም ግለሰዎች፣ ተቋማት እና ሀገራት በቀላል ችግሮች ዙሪያ ውስብስብነትን በመገንባት መፈታት የማይችሉ እንዴት እንደሚያስመስሉ ለማሳየት የሚያገለግል ምፀታዊ ዘዴ ነው።
እውነታን በግልፅ ከመቀበል ይልቅ፣ የተወሳሰቡ ማብራሪያዎችን፣ ማለቂያ የሌላቸው ከእውነታው ጋር ዝምድና የሌላቸው ስትራቴጂዎችን እና ውድ የሆኑ አንፀባራቂ ማትለፊያዎችን ይፈጥራሉ—ይሁን እንጂ መሠረታዊው ጉዳይ አንድ ነው፦ ፈረሱ ሞቷል።
ቀላሉ ሀሳብ፡
የሞተ ፈረስ እየጋለብክ መሆኑን ከተገነዘብክ፣ ማድረግ የምትችለው የመጨረሻው የብልሆች ውሳኔ ቢኖር ወዲያው ከዛ ፈረስ ጀርባ መውረድ ነው።
ነገር ግን በተጨባጩ ዓለም ውስጥ፣ ብዙዎች እውነታውን መቀበል ስለሚከብዳቸው ግራገብና አጥፊ መንገዶችን የሚመርጡበት ውሳኔዎች ይወስናሉ፣ እውነታውን የሚደብቁ ቆሻሻም ሆኑ ውብ ነገሮች ሁሉ ይጥፋሉ።
ይሄንን ውሳኔያቸውን ተከትለው ሰዎች የሚያደርጉት አስገራሚ ድርጊቶች
1) ፈረሱን እንደገና ጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ ኮርቻዎችንና ቁሳቁሶችን ይገዛሉ ያለብሱታልም።
2️) ፈረሱ በህወት እንዳለ በማሰብ ልዩልዩ የፈረስ ስንቅ ያቀርባሉ እጅግ ብዙ ሀብት ሁሉ በእንዲህ ያለው ከንቱ ተግባር ላይ ያፈሳሉ።
3) ጉዳዩ ከመሪነት ነው በሚል ሀሳብ ፈረሰኛውን ይቀያይራሉ።
4) የሞተው ፈረስ ፍጥነት እንዴት እንደሚጨምር መፍትሄ ለማበጀት ለዓመታት በርካታ ስብሰባዎችን ይጠራሉ በአንድ ስብሰባ ለወራቶች ይቀመጣሉ በርካታ ውይይቶችን ያደርጋሉ ይከራከራሉ የተቃወመውን ያጠፋሉ መፍትሄ መሳይ የጥፋት ውጥን ላይ ይረባብባሉ።
5) ጉዳዩን “ለመተንተን” ኮሚቴዎችን ያዋቅራሉ ሐሳዊ-ምሁራንን ያደራጃሉ አዋቂ-መሳይ ደጋፊዎቻቸውን ይጠራሉ
እና የተለዩ የጥፋት ቡድኖችን ይፈጥራሉ የጥፋት ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ።
6) አዋቂ መሳዮችም ፈረሱን ለማጥናት ወራቶች ይወስዳሉ፣ ቀድሞ የሚታወቀው የፈረሱን መሞት በተለየ ቃላት ይገልፁታል።
7) ሐሳዊ-ምሁራንም የሞተው ፈረሳቸውን ከሌሎች ሙታን ፈረሶች እንዴት እንደሚለይ ያወዳድራሉ ይተነትናሉ ያመሳጥራሉ ውድቀታቸውን justify ለማድረግ ብዙ ርቀት ይሄዳሉ ውድቀታቸውን ተስፋ ባላቸው ቃላት ለመደገፍ ይጣጣራሉ። “ውድቀትን መደገፍ የከፋ ውድቄትን ይጠራል” የሚሏቸውን ይገድላሉ ያስራሉ ያስወግዳሉ ያስነውራሉም።
😎 ፈረሳቸው ልዩ ስልጠና እንዲያገኝ ያደርጋሉ፣ analytically ክህሎት ከሞት እንደሚመልስ በማሰብ። አዳዲስ ትግሎችንም ይነድፋሉ። “ትግል ከሞት የመመለስ አቅም የለውም መፍትሄችሁ ኢተፈጥሯዊ ነው አዳዲስ ችግሮችን ይወልዳል” የምሏቸውን ሁሉ ይገድላሉ ያስራሉ ያስነውራሉ ያዋርዳሉም።
9) ለዚያ ስልጠና በጀት ዲስኩር ያዘጋጃሉ — የበለጠ ሀብት ያቃጥላሉ የበለጠ ህይወት ያጠፋሉ የበለጠ ችግር ይተክላሉ የበለጠ እሴት ያፈርሳሉ የሌሎች መጠቀሚያም ይሆናሉ። ወደየትም የማይወስድ ትግል ቀይሰው በትግሉ ሂደት በከንቱ የሞቱትን ሁሉ “መስዋእትነት የከፈሉ” በሚል በከንቱ ያከብራሉ ሲያከብሩም ይኖራሉ። ከህይወት ካሉት ሞታኑ በልጠው አገሩ በደምና በክፋት ቢጨቀይም እነሱ ግን “ፈረሳችን-መስመራችን” እያሉ ሦስት ትውልዶችን ጨርሰው ለአራተኛ ይዘጋጃሉ።
የክህደት የላይኛው ደረጃ
በመጨረሻም፣ እውነታን የመካድ ደረጃቸው በዝቶ ወደ አስቂኝ የእብደት ደረጃዎች ይሸጋገራል። እውነታን ከመቀበል ይልቅ ፈረሳቸውን በህይወት መኖሩን ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ለማሳመን “ሞት” የሚለውን ትርጉም እንደገና redfine ያደርጋሉ። ይህ ዓይነቱ አዕምሯዊ ውቅር የማያቋርጥ ግጭትና የብዥታ አዙሪት ውስጥ ያስኖራቸዋል።
ዓለም ውስጥ በዚህ ወጥመድ ውስጥ የገቡ ምን ያህል ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግስታት አሉ የሚለውን ጥያቄ ባልመልስም ህወሓት ግን አውራቸው ነው። ተጨባጩን እውነታ መቀበል አቅትዋቸው በምቾት የብዥታ አዙሪት ውስጥ ሲሽከረከሩ እልፍ ጥፋቶችን እየፈበረኩ የሚውሉ። አንዴ ከምቾታቸው ደብር ላለመውጣት ስንት የጥፋት ዲር ሲያደሩ የሚውሉ። ስንት ትውልድ አጥፍተው ተጨማሪ ትውልድ ለማጥፋት የሚሰናዱ!!
ጊዜ፣ ሀብት፣ ህይወት፣ ማህበረሰብ፣ አገር፣ እሴት ሁሉንም ያጠፋሉ። በመጨረሻም እያለቀ የሚሄድ እሴትየለሽ ተስፋየለሽ መሃን ማህበረሰብን ይፈጥራሉ። ይህም እውን ለማድረግ ጫፍ ላይ ደርሰዋል።
እውነታን የመቀበል ዊዝደም ያለው አዕምሮ ግን፡ አንድ ሲስተም ወይም ስርዓት function ማድረጉን የሚቋረጥበት ለይቶ ማወቅ ይችላል። ይህች ነጥብ “point of no return” ይሏታል። አንድ መንግስታዊ ስርዓት ስርዓት ሆኖ መቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ከተቋረጠ ወደ የሬሳ ፋብሪካነት ነው የሚሸጋገረው። ህወሓት የገነባው ስርዓት ይሄንን እጣፈንታ የደረሰው ገና ደደብት በወረደ ማግስት ነበር። በመሆኑም ለ15ዓመታት ሙሉ የትግራይ ንጉሳዊ ቤተሰቦች በማፅዳት ኖረ። በመቶሺዎችን ጨረሰ አፀዳ።
ከሞተው ጋር ተጣበቆ መቀጠልን ምርጫው ያደረገ ሁሉ እጣፈንታው ከሞት የባሰ ውርደትና ምስቅልቅል ነውና የትግራይ ህዝብ በውሸት ፕሮፖጋንዳ ውጭ በሞት ውስጥ ኖረ።
ይሄንን የተረዳቸው አዕእምሮዎች ቁጥራቸው በእጅጉ እየደገ ቢሆንም አሁንም የትግራይ ህዝብ ከሞተው ጋር ተጣብቆ እንዲያልቅ የሚፈልጉ ህወሓት መነፀር ለባሽ መዥገሮችን ተፈጥሯል!!
የመቀበል መርህ
ችግርን ከስርመሰረቱ መቀበል ድክመት አይደለም፤ ወደ እውነተኛ መፍትሄዎች የሚወስድ የመጀመሪያው እርምጃ እንጂ። እውነታን ከተቀበልክ በኋላ አዲስ እድል ብቅ ይላል፣ አዳዲስ ስትራቴጂዎችና ሕያው መፍትሄዎች ላይ ኃይልህን መለማመድ ትችላለህ። ከሞተ ፈረስ መለየት ማለት በትከሻህ ላይ ያለውን እድገት ማግኘት፣ በእዕምሮህ ውጥ ያለው ምኞት መጨበጥ፣ ሙሉ አቅምህን የመጠቀም ወለል ላይ እንደልብህ እንደመንቀሳቀስ ነው።
እውነታውን መቀበል ስትችል ብቻ ነው ኢነርጂህን ወደ ትኳኩስ እድሎች፣ አዳዲስ ስትራቴጂዎች፣ አዳዲስ አደረጃጀቶች እና ህያው መፍትሄዎች redirect ማድረግ የምትችለው። ከሞተው ፈረስ ጋር ተጣብቆ ለውጥን መገደብ ኩሬ እንደመሆን ያለ ነው። ኩሬ መታደስ ስለማይችል ጥንብ ነው ማእከሉ የሙታን ስብስብ ነው። ጥንብአንሳዎች ብቻ የሚመላለሱበት የሙታን ሰፈር ይሆናል። በመጨረሻም ከህይወት ከተሰፋ ወጥቶ በውጭ ኃይሎች ግፊት ተደፍኖ ይከስማል። ቅሪቶችን የሚመገቡ የገዛዘፉ መጤ ዛፎችም ይበቅልበታል።
በመጨረሻም
የሞተው ፈረስ ፅንሰ-ሀሳብ ከምፀአታዊም በላይ ነው — ማስተካከያ ማሳያ መስታውት ነው።
ይህ ንድፈሀሳብ ለሁላችንንም እንዲህ ይጠይቃል፡ በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት የሞቱ ፈረሶችን ነው አሁን ድረስ የምንጋልበው? ከህፃንነታችን ጀምሮ ሲነገሩ የኖሩትን የውሸት ማንነት መገንቢያ የህወሓት-ኦነግ ትርክቶች፣ ከሁሉም መልካም ነገሮች ጨምድደው የሚያስቀሩን ልማዶች? የወደፊት ተስፋ የሌላቸው ሙያዊ ትምህርቶች? ፍሬብስ ስትራቴጂዎች? የተመረዙ ግንኙነቶች?
ይህ ፅንሰሀሳብ ወደህይወት መመለስ በማይችለው ላይ ህይወት እንዳናባክን ይመራናል። ከሙታን ተነጥለን፣ ከላይ ወርደን፣ ወደፊት አንድንገፋ ወደ አጓጊው ህይወት እንድቀሳቀስ በብርታት ይጠራናል። ይህንን ስናደርግ እሴቶቻችንን ሀብታችንን ጥበባችንን እና ራዕይችንን በእውነት ሕያው እና ፍሬ በሚሰጥ ነገር ላይ እናውላለን።
መጀመሪያ ግን የምትጋልበው ፈረስ ሙት መሆኑን አስተውል። ቀጥሎም ከዚህ ፈረስ ጀርባ በመውረድ የመጀመሪያው እርምጃህን ውሰድ። ቀጥሎ የሞተውን ፈረስ በመቅበር ለአዲስ ተስፋና ስርዓት ተዘጋጅ። እዚህ ምእራፍ ላይ ከደረስክ ብቻ ነው ወደቀጣይ መፍትሄ መሸጋገር የምትችለው።
የህወሓት ችግር ፈፅሞ የአመራር ችግር አይደለም። የህወሓት ችግር እንደርጅት የተመሰረተበት ፖለቲካዊ ፍሬምወርክ ነው። መለስ ዜናዊ ሲመራው የኖረው ህወሓት ስልጣን ላይ በመሞርከዙ ትክክል ይመስል ነበር። እንዴት ያሉ ኢሚዛናዊ መዋቅሮችን፣ ኢ-ሉአላዊ ውሳኔዎችን እና ኢ-ህጋዊ ሕገመንግሥትን እንዳፀደቀ ተመልከቱ። በመጨረሻም እስካሁን የተከፈለው መስዋእትነት ሁሉ እንዴት በአፍጢሙ እንተደፋ ተመልከቱ። ይህ ሁሉ የሞተውን ፈረስ ለማስቀጠል ነበር። በመሆኑም ህወሓት ደብረፅዮን ይምራት ጌታቸው ረዳ ወይም እየሱስ ክሪስቶስ ይምራት ተዓምር እስካልተጠቀመ ድረስ የሞት ፋብሪካ መሆኗ ፈፅሞ የማይቀር ነው። እስካሁን በህወሓት የየተገነቡ ስነልቦናዎች፣ የተዘረጉ መዋቅሮች፣ የፀደቀው ህገመንግስት፣ የተፈበረኩት ባንዲራዎች ጭምር መፍረስ አለባቸው። አለያ ግን መልኩ እየቀያረ ይጥላል ውጤቱም ከላይ እንደገለፅኩት ይሆናል።
ከሞተ ፈረስ ላይ ውረዱ!! stop wasting generations on lost cause !!
Engineer Tafere Hiluf

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top